ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አንድ ስምንተኛ ጨዋታውን ከሴራሊዮን አቻው ጋር ይጫወታል። 

የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ 10 ሰዓት ላይቤሪያ ሞኖሮቪያ የሚገኘው ሳሙኤል ካንዮን ዶ ስታዲየም ይካሄዳል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ ሰባተኛ ጨዋታው በግብጽ አቻው 2 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።

ውጤቱን ተከትሎ ቡድኑ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ በሂሳባዊ ስሌት ከዓለም ዋንጫ ውጪ መሆኑ ይታወቃል። 

ተጋጣሚዋ ሴራሊዮን በዘጠኝ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ባለፈው ሳምንት ባደረገችው የምድቡ ሰባተኛ ጨዋታዋ ከጊኒ ቢሳው ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች።

ኢትዮጵያ እና ሴራሊዮን በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

የዛሬው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በአንጻሩ ሴራሊዮን ከምድቡ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ለማድረግ የሚያስችል እድል ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

በዚሁ ምድብ ቡርኪናፋሶ ከግብጽ ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በኦገስት 4 ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ቡርኪናፋሶ በ14 ነጥብ ሁለተኛ፣ ግብጽ በ19 ነጥብ የምድቡ መሪ ናት።

በጨዋታው ግብጽ ካሸነፈች ሁለት ጨዋታ እየቀራት ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረግጣለች። 

በአንጻሩ ቡርኪናፋሶ ድል ከቀናት ለዓለም ዋንጫ የሚያልፈው ሀገር በመጨረሻ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ይወሰናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም