ቀጥታ፡

በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመከላከል የጋራ ትብብርን ማጠናከር ይገባል  

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የጋራ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ "ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በጉባኤው መክፈቻ የታደሙት የተለያዩ አገራት መሪዎችም በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመከላከል የጋራ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሃሙድ አሊ የሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን በብዙ እየፈተነ ይገኛል።


 

ይህን ዓለምአቀፋዊ ተግዳሮት ለመከላከል አህጉሪቷ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗንም አንስተዋል።

ይሁንና አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት በቂ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የባለሙያ ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ያላት ድርሻ አነስተኛ መሆኑን ያስታወሱት  የኮሚሽን ሊቀ መንበር መሃሙድ፤ ሆኖም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆኗን አመልክተዋል።

አህጉሪቷ ዓለምአቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ሁለንተናዊ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ፍትህን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በናይሮቢ በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሄው አካል ለመሆን በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አቅጣጫ ማስቀመጧን አስታውሰዋል።


 

አህጉሪቷ የችግሩ ዋነኛ ተጎጂ እንደመሆኗ ጉዳቱን አስቀድሞ ለመከላከል አሰላለፏን መቀየር ይገባታል ነው ያሉት።

በአፍሪካ ለአየር ንብረት ተስማሚ ኢኮኖሚ ለመገንባት አገራት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አገራት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ዓለምአቀፍ ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በዓለምአቀፍ መድረኮች ለማስተጋባት የተቀናጀና የተናበበ የጋራ ሥራ መስራት የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሀሙድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እንድንመክር መድረክ ስላዘጋጀ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።


 

አገራቸው ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ያላት አስተዋፅኦ አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ሶማሊያ ትብብሯን አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።

ለዚህም ፖሊሲ በመቅረጽና ተቋማዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እንዲሁም የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ በማቋቋም የተግባር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም