ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር አሳይታለች

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በህዳሴ ግድብ ለአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ማሳየቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

"ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ጀምሯል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካውያን አፍሪካዊ መፍትሔ የምናዘጋጅበት ነው ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፣ በትብብር የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ አፍሪካ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ እና የጊዜ እጥረት እንዳለባት ተናግረዋል።

አፍሪካ ታዳሽ ሀይል፣ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ውሀና ጸሀይ ሀይል ያላት አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።


 

ስብሰባው በህልውናችን ላይ ለመምከር ሳይሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት ወሳኝ ወቅት ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን እርዳታ እንደማንፈልግ እንዲያውቁልን እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለራዕዮች በመሆናችን ከእኛ ጋር ሊያለሙ ይገባል ብለዋል፡፡

ራዕዩን ወደ ተግባር ለመቀየር የአፍሪካ የአየር ንብረት ኢኖቬሽን ኮምፓክት ይፋ እንዲሆን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2019 በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን አንስተዋል፡፡

በዚህም ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ማስቀረት፣ የአካባቢን ስነ ምህዳር መጠበቅ እና የአረንጓዴ ልማትን ማሳደግ ችላለች ብለዋል።

አፍሪካ ከንግግር ያለፈ የሚጨበጥ የተግባር እርምጃ ያስፈልጋታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን ምርት በመቀነስ የገጠሩን ማህበረሰብ ገቢ ማሳደግ ችላለች ብለዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት በቅርቡ እንደምታስመርቅ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ኢኒቬቲቮች ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በራሷ የወሰደቻቸው የመፍትሔ ርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና ህዳሴ ግድብን በመገንባት የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር አሳይታለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም