ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚደነቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚደነቁ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አዲስ ተመራጮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አዲስ ተመራጮች በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በዚህም የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ አውደርዕይ እና ብሔራዊ ቤተ-መንግስትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ በጉብኝቱ በተመለከቱት ነገር መገረማቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተከናወኑ ስራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተዓምር መሆናቸውን አንስተው ትልቅ ለውጥ ማሳየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የልማት ሥራዎቹ ለመጭው ትውልድ ትልቅ ትሩፋት የሚሆኑ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከጎበኟቸው ሀገራት የተሻሉ የልማት ስራዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በለውጡ መንግስት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቁመው አስደናቂ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ኢማም ሀጂ አብዱልሃዲ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ጋሊ ሙክታር በአዲስ አበባ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባል አዩብ ደርባቸው የልማት ሥራዎቹ ሀገርን በመገንባት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ለመጭው ትውልድ የሚተላለፉ ድንቅ ስራዎች ናቸውም ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼህ አደም አብዱልቃድርም የልማት ሥራዎቹ በርካታ ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡