ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የሪፎርም ስራዎች አስተማማኝና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት መሰረት የጣሉ ናቸው-ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የሪፎርም ስራዎች አስተማማኝና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት መሰረት የጣሉ ናቸው-ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተተገበሩት የሪፎርም ስራዎች አስተማማኝና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት መሰረት የጣሉ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ጳጉሜን 3 የእመርታ ቀን "እመርታ ለዘላቂ ከፍታ " በሚል መሪ ሃሳብ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት በማሳየት በሳይንስ ሙዚየም በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የእመርታ ቀን በቀጣይ ባሉ ጊዜያት የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት ተስፋ የሚሰነቅበት ነው።
ባለፉት የለውጥ አመታት ተግባራዊ በተደረጉት ቁልፍ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ፣የማዕድን፣ የገቢ አሰባሰብና ሌሎች ማሻሻያዎች ተጨባጭ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚሁ ወቅት የታዩት ሁለንተናዊ ለውጦች ኢትዮጵያ ከሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በኋላ የምትደርስበትን ከፍታ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉ የዋጋ ግሽበትን፣ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን እና አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እያስቻለ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ከመሰብሰብ አኳያ ትልቅ እመርታ መመዝገቡን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተገኘ ያለውን ስኬት ለማስቀጠልና ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው እንደገለጹት ፤ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደምትሰለፍ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንኑ ትንበያ ስኬታማ ለማድረግም በተለይ የግል ዘርፉ ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።
ኢትዮጵያን በታቀደው የእድገት ደረጃ ለማድረስ አሁን የተጀመረው የካፒታል ገበያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
መንግስት ባለፉት ጥቂት አመታት ያደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርም የግል ዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ የዋሪት ሙሉ ጥላ ዋና ስራ አስኪያጅ ትህትና ለገሰ ናቸው።
በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ይገጥም የነበረውን ችግር ከማቃለል አንፃር በሪፎርሙ የተከናወኑት ተግባራት ለግል ባለሃብቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የእመርታ ቀንን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር በጋራ አክብረውታል።