የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ ድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ ድል ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትየጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ ድል መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላለፉት 14 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን እውቀት፣ ጉልበትና ጥሪት ተገንብቶ ለስኬት መብቃቱ የመቻልን አቅም ያሳየንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ፤ የግድቡን የግንባታ ሂደትና የሚኖረውን ሀገራዊ ፋይዳ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የግድቡ የግንባታ ሂደት ብዙ ጫናዎች የነበሩበት መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አረጋዊ፤ በመንግስት ፅኑ አቋምና ቁርጠኝነት እንዲሁም በህዝቡ ያላሰለሰ ድጋፍና ትብብር ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ የሀገር ሃብት መሆኑን አስረድተዋል።
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት ብስራት መሆኑን አንስተው በቀጣይ ግዙፍ የልማት ስራዎችን በማከናወን በራስ አቅም ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ፤ ኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የመገንባት ህልሟን እውን እያደረገች መሆኑን አንስተው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የምታገኝ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።