ኤግዚቢሽኑ በንድፈ ሐሳብ ያገኘነውን እውቀት በተግባር ያየንበት ነው - የኢትዮ ስፔስ እና ስፓሻል ኪድስ ክለብ ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
ኤግዚቢሽኑ በንድፈ ሐሳብ ያገኘነውን እውቀት በተግባር ያየንበት ነው - የኢትዮ ስፔስ እና ስፓሻል ኪድስ ክለብ ሰልጣኞች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር ያዩበት እና ለተሻለ የቴክኖሎጂ የምርምር ስራም የሚያነሳሳቸው መሆኑን የኢትዮ ስፔስ እና ስፓሻል ኪድስ ክለብ ሰልጣኞች ገለጹ፡፡
አምስት የዐውደ ርዕይ ምድቦችን የያዘው የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ መከፈቱ ይታወሳል።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ግብርና ቴክኖሎጂ፣ የውኃ ኃይል እና ኢነርጂ፣ ኤሮኖቲክስ እና አቪዬሽን ላይ ያተኮሩ የዐውደ ርዕይ ምድቦችን ይዟል።
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በክረምቱ ወራት በኢትዮ ስፔስ እና ስፓሻል ኪድስ ክለብ ለበርካታ ሰልጣኞች በስፔስ ሳይንስ፣ አስትሮኖሚ፣ አስትሮ ፊዚክስ፣ ኤሮ ስፔስ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ሮቦቲክስ እና በሌሎችም ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ይህንንን ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ስልጣኞችም የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን የጎበኙ ሲሆን በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኤግዚቢሽኑን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ስልጣኞች እንዳሉት፤ ጉብኝቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ቴክኖሎጂዎችን በተሻለ መንገድ ለማየት እንደረዳቸው ተናግረዋል፡፡
በቋሚ ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ዕድገት እያመራች መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኤሮ ስፔስ፣ በግብርና ቴክኖሎጂና የውኃ ኃይል ዘርፍ ተግባር ተኮር እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ለተሻለ ፈጠራ እንደሚያነሳሳቸው ጠቁመው መጪውን ጊዜያቸውን ብሩህ ማድረግ የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ራዳር የሚል የፈጠራ ፕሮጀክት በመስራት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ታዳጊ ሚካኤል አሸናፊ ኤግዚብሽኑ በፈጠራ ስራው ላይ ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማከል እንደረዳው ተናግሯል፡፡
የግብርና ዘርፉን ማዘመን የሚያስችል የፈጠራ ስራ በመስራት ላይ መሆኗን የገለጸችው ታዳጊ ሶሊያና አብዱረሃማን ጉብኝቱ ተጨማሪ ዕውቀት እንድታገኝ እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡
በግብርናው ዘርፍ አንድ ማሽን ሁለትና ከዚያ በላይ ተግባራትን በማከናወን የአርሶ አደሩን ስራ ማዘመን የሚያስችል የፈጠራ ስራ በመሥራት ላይ እገኛለሁም ብላለች፡፡
በጉብኝቱ ከተመለከቷቸው ባሻገር በሌሎች ዘርፎች የፈጠራ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያነሳሳቸው ጠቁመዋል፡፡
በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ተመራማሪ እና በኢትዮ ስፔስ እና ስፓሻል ኪድስ ክለብ አስተባባሪ ኢንጅነር አልዓዛር ስዩም በበኩላቸው፤ ሰልጣኞቹ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መጎብኘታቸው ለተሻለ የፈጠራ ሃሳብ ያነሳሳቸዋል ብለዋል፡፡
ጉብኝቱ ሰልጣኞቹ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያገኙትን እውቀት በተግባር ተመልክተው የተገነዘቡበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡