በምግብ ራስን ለመቻል በስንዴ ልማት ላይ የመጣውን አበረታች ውጤት ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በምግብ ራስን ለመቻል በስንዴ ልማት ላይ የመጣውን አበረታች ውጤት ማጠናከር ይገባል
ወልመራ ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፡- በምግብ ራስን ለመቻል በስንዴ ልማት ላይ የመጣውን አበረታች ውጤት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የእመርታ ቀንን ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ የስንዴ ክላስተር ጉብኝትና የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ፣ አባ ገዳዎች እና ሃዳ ስንቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ድዳ ጉዳታ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልልና በዞኑ ብሎም በሀገሪቱ በአብሮነትና በአንድነት ጠንክሮ በመስራት በየዘርፉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይም በምግብ ራስን ለመቻል ሲካሄድ በቆየው የስንዴ ልማት ስራ አበረታች ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬትንም አንስተዋል። ይህንን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የወልመራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ድዳ ጋር በበኩላቸው፤ በወረዳው ደረጃውን የጠበቀ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
የወረዳው አርሶ አደሮች በክላስተር ስንዴ በማምረት በውጤታማነት መቀጠላቸውንም አውስተዋል።