የህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ለሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንድንነሳሳ ያደርገናል- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ለሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንድንነሳሳ ያደርገናል- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
ደሴ ፤ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ለሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንድንነሳሳ ያደርገናል ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ነዋሪዎቹ እንደገለፁት፤ ለህዳሴ ግድቡ በተለያዩ መንገዶች አስተዋፅኦ በማድረጋችን ለልጆቻችን ዘላለማዊ አሻራ ከማኖራችን ባለፈ ከምንጊዜውም በላይ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው።
ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሼህ አህመድ አረቡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የቁጭታችን ውጤት፣ የታላቅነታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
እድገታችንን የማይሹ የውጭ ሃይሎችን ጫና ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶችን ተቋቁመን ለምረቃ በመብቃቱ በቀጣይ ለሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአንድነት እንድንነሳሳ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ለግድቡ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው በቀጣይም የታቀዱ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።
ሌላዋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሉባባ ሁሴን በበኩላቸው፣ ለህዳሴ ግድቡ 20 ሺህ ብር የሚጠጋ ድጋፍ በማድረግ ለልጆቼ አሻራ አስቀምጫለሁ ነው ያሉት።
የግድቡ መጠናቀቅ ከተባበርን የማናልፈው ችግርና ፈተና አለመኖሩን ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመው እልህ አስጨራሽ ጊዜን አልፎ መጠናቀቅ በመቻሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በከተማችን እያጋጠመ ያለውን የመብራት መቆራረጥ ችግር በመቅረፍና ለገጠሩ ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽ በማድረግ ለውጥ እንደሚያመጣም አመልክተዋል።
የሁላችንም አሻራ ያረፈበት፣ የአንድነታችን ማህተም፣ የሉዓላዊነታችን ማረጋገጫ የሆነው ግድብ በመጠናቀቁ ደስታችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፈረጃ ሱሌማን ናቸው።
በግሌ ካደረኩት ድጋፍ በተጨማሪ በአካባቢዬ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር አሻራቸውን እንዲያኖሩ ማድረግ በመቻሌ ግድቡ ሲጠናቀቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምርቃት በመቃረቡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።