ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ ወደ ኋላ የሚጎትታት ነገር እንደሌለ ያሳየንበት ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ  ወደ ኋላ የሚጎትታት ነገር እንደሌለ ያሳየንበት ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ዓባይን አልምቶ ለሀገሪቱ እድገት ማዋል አለመቻላችን የዘመናት ቁጭታችን እንደነበረ አንስተዋል።

ይህን ቁጭት ለመቀየርም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በራስ ሀብትና አቅም ማጠናቀቅ ችለናል ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ  ዜጎች ለአንድ ግብ ከተባበርን ብሄራዊ ጥቅማችንን ከማረጋገጥ  ወደ ኋላ የሚጎትተን ነገር እንደሌለ ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

መንግስት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ በርካታ የልማት ስራዎችን አቅዶ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዜጎች በህብረት ከቆምን ልማትን ማፋጠን እንደምንችል በህዳሴ ግድብ አረጋግጠናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው  በቀጣይም የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ በሚሰሩ ተግባራት ላይ ዜጎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ብዝሃነት ጎልቶ የሚንጸባረቅባት፣ የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ ይህን ወደ ልማት ለመቀየር ጠንካራ ስራ መስራት አለብን ሲሉ አክለዋል።

የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ምሳሌ የሆነ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም