በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው
ባሕርዳር፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ፈተናዎችን በስኬት በማለፍና በፅናት በመቆም በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ ግብርና፣ ገንዘብ፣ ገቢዎች፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ ፕላንና ልማትና ማዕድን ቢሮዎች የእመርታ ቀንን በባሕር ዳር ከተማ በጋራ አክብረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ የእመርታ ቀን ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ባስመዘገብንበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ መሆን የተቻለው ክልሉ ፈተናዎችን በስኬት በማለፍና ሌት ተቀን በመስራት እንደሆነም ገልጸዋል።
በዚህም የልማት ምንጭ የሆነውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱና ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት አልምቶ ለክልሉ እድገት መጠቀም መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በግብርናው ዘርፍም የሚመረተው ምርት ለወጭ ንግድና ለፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ ግብአት ላይ እንዲተኮር በማድረግ የተሳሰረ የአመራረት ስልት መከተል መቻሉን አንስተዋል።
እንደ ሀገር ሲታይ የዲፕሎማሲ አቅማችን ያደገበትና ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ስኬታማ በሆነበት ወቅት ላይ መገኘታችን የእመርታ ዘመን ነው ብለዋል።
የእመርታ ቀንን ስናከብርም በሁሉም የልማት መስኮች እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን በመገምገም አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
በአከባበሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።