ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን በመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ይገባል - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

መቀሌ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን መፍታትና እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበት የቅድመ ምክክር መድረክ በመቀሌ አካሄዷል።

በዚህም ኮሚሽኑ በክልሉ የምክክር ሂደቱን ለመጀመር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኮሚሽነሩ በሰጡት ማብራሪያም፤ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በምክክር ችግሮችን በመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዞና ልብ ለልብ ተገናኝቶ መጓዝ ይገባል ሲሉ አንስተዋል።

በመሆኑም በሀገራዊ ምክክሩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በምክክር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይገባል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የቅድመ ምክክር መድረክ ለዚሁ ስኬት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልፀዋል።

ለችግሮች ሁሉ ቁልፉ መፍትሄ ምክክር በመሆኑ እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳተፊዎችም ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በዘላቂነት ለመፍታት ዝግጁ ስለመሆናቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቀደም ሲል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ውይይት መደረጉን መግለፃቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም