ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች በሁሉም መስኮች እመርታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፡- በለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች በሁሉም መስኮች እመርታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ጳጉሜን 3 የእመርታ ቀንን አስመልክቶ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተኪ ምርት፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ያላቸውን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም የበላይነህ ክንዴ የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ ኤ ኤም ጂ ሆልንዲንግስና ቢጃይ ኢትዮ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኢንጂነሪንግ ሶሉሽንስን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት፤ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ውጤት እንዲመዘገብ መሰረት ጥሏል።

ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ትልቅ አቅም መፍጠራቸው እየተመዘገበ ላለው እመርታ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ አምራች ዘርፉን የሚያበረታቱ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው ተጠቃሽ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉ ይበልጥ እንዲነቃቃ እያደረገ ነው ያሉት አቶ መላኩ በውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና የብድር አቅርቦትን ጨምሮ የተከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ለአምራች ዘርፉ መጠናከር አወንታዊ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉንም አስረድተዋል።


 

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት፤ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ያለው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ታክስ የመሰብሰብ አገራዊ አቅም እያደገ መጥቷል።

በ2011 በጀት ዓመት 200 ቢሊዮን ብር የማይሞላ ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት ከ900 ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ውስጥ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማደግ ጋር ተደምሮ የመጣ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ እምርታ ከተመዘገበባቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ እሴት የተጨመረበት ቡናን ወደ ውጭ የመላክ ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ አንስተዋል።

ለዚህም አርሶ አደሮችና በቡና ማቀነባበር ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሀመድራፊ አባራያ እንዳሉት፤ ከለውጡ በኋላ የማዕድን ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት የተሰጠው ትኩረት በመስኩ ውጤት እንዲመጣ አስችሏል።


 

አገራዊ አቅም የሚፈጥሩ ትልልቅ የማዕድን ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ፤ ተቋማት ተቀናጅተው በእቅዳቸው መሰረት እንዲሰሩ መደረጉ በየዘርፉ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን አስረድተዋል።


 

ለዚህም ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተቋማት ተናበው እንዲሰሩ ድጋፍና ክትትል ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የላቀ ውጤት እንዲመጣ መደላደል መፍጠሩን አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም