ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት በዓላማ ጽናት ተግዳሮቶች ታልፈው አመርቂ እመርታዎችን ማስመዝገብ ተችሏል - የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2017(ኢዜአ)፦በለውጡ ዓመታት በመተባበር እና በዓላማ ጽናት ተግዳሮቶች ታልፈው አመርቂ እመርታዎችን ማስመዝገብ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ጳጉሜን 3 የእመርታ ቀን  "እመርታ ለዘላቂ ከፍታ " በሚል መሪ ሃሳብ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት በማሳየት በሳይንስ ሙዚየም በፓናል ውይይትና በሌሎች ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል። 


 

ቀኑን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር በጋራ እያከበሩት ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በመተባበርና በዓላማ ጽናት ተግዳሮቶች ታልፈው አመርቂ እመርታዎችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ለዚህም በየዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች ማሳያ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን የኢኮኖሚ ስኬቶች ለማወጅ ትክክለኛ ወቅት ላይ ትገኛለች ነው ያሉት።

የሪፎርሞቹ ዋና ዓላማም ይሄን የኢትዮጵያን እመርታ መሸከም የሚችሉ ተቋማት እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አስተማማኝና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንዲገነባ መሠረት ጥለዋል፤ በቁልፍ የልማት ዘርፎች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በገቢ አሰባሰብና በሌሎችም መስኮች ተጨባጭ ዕድገት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

ገቢን እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ የወጪ ንግድ ገቢ እንዲያድግ በማድረግ፣ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የእመርታ ቀንን የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ምኞት የሆነውን ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ስምምነት በተፈረመ ማግስት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሆኖ በመረባረብ የገባነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በምናስመርቅበት ዋዜማ ላይ የምናከብር መሆኑ ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተከበረ ሲሆን፤ ባለፉት ሰባት የሪፎርም ዓመታት የተገኙትን አስደናቂ ውጤቶች የሚያሳዩና ሀገራዊ ዕድገቱን የሚያንፀባርቁ ሁነቶች ቀርበውበታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም