ቀጥታ፡

ባንኩ በደብረ ብርሀን ከተማ ለ200 አቅመደካሞችና አረጋውያን ማእድ አጋራ

ደብረብርሃን ፤ጳጉሜ 3/2017 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በደብረ ብርሀን ከተማ ለ200 አቅመደካሞችና  አረጋውያን  ማእድ አጋራ።  

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት ባንኩ በሚሰጠው አገልግሎት በከተማው ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መፋጠን የጎላ አስተዋጾ እያበረከተ ነው።

አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የፈጸመው ተግባር አርአያ መሆኑን ተናግረው፣ለድጋፉ አመስግነዋል ።


 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረብርሀን ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ጨበር እንደገለጹት ባንኩ ከመደበኛ ተግባሩ በተጨማሪ በአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችም ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፈነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ 200 አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ግምት ያለው ማእድ  ማጋራት አድርጓል ብለዋል።

በነፍስ ወከፍ የተደረገው ድጋፍ 25 ኪሎግራም የዳቦ ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይት፣ በጥሬ ገንዘብ  1 ሺህ 300 ብር እንዲሁም  ለልጆቻቸው ደብተርን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑ መካከል  አቶ ተክሌ ሞገስ እንዳሉት የተደረገላቸው ድጋፍ በአሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል ።

ወይዘሮ በቀለች ደስታ በበኩላቸው በአዲስ  ዓመት በዓልን አስመልክቶ የተደረገልኝ ድጋፍ ከቤተሰቦቼ ጋር ተደስቼ ለማሳለፍ ያስችለኛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም