የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ በለውጡ መንግሥት ምላሽ አግኝቷል-ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ በለውጡ መንግሥት ምላሽ አግኝቷል-ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ በለውጡ መንግሥት ምላሽ አግኝቷል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
ህዝበ ሙስሊሙን በታማኝነት ለማገልግል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ የመጅሊስ ምርጫ ሂደት የማጠቃለያ መርሃ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዘንድሮው የመጅሊስ ምርጫ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ በለውጡ መንግስት ምላሽ አግኝቷል ብለዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተዋረዳዊ የምርጫ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ የመንግስት ተቋማትና ተባባሪ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ህዝበ ሙስሊሙ የሰጣቸውን ታላቅ አደራ በታማኝነትና በውጤታማነት ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ ስኬታማ ሆኖ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምክር ቤቱ በሥራ ዘመኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት በመግለፅ፥ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ለምክር ቤቱ ስራ መሳካት አብሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ አብዱላዚዝ ኢብራሂም (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የ2017 የመጅሊስ ምርጫ ከነሐሴ 9 ቀን 2017 ጀምሮ በስኬት ተከናውኗል።
በምርጫው ጠቅላይ ምክር ቤቱን የሚመሩ ፕሬዝዳንት፣ምክትል ፕሬዝዳንትና ጸሐፊን ጨምሮ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚዎች መመረጣቸውን ተናግረዋል።