ቀጥታ፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተግባር የታየው ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሌሎች የልማት ስራዎችም ማስቀጠል ይገባል

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በተግባር የታየውን ህብረ ብሔራዊ አንድነት በሌሎች የልማት ስራዎችም አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰባት የፌዴራል ተቋማት በጋራ ያዘጋጁት ኹነት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬን (ዶ/ር) ጨምሮ የልዩ ልዩ ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና ከሁሉም ክልሎች የመጡ የባህል ቡድን አባላት የተሳተፉበት የእግር ጉዞ ተደርጓል።

የኢትዮጵያን አንድነት፣ አብሮነትና ህብረ-ብሔራዊነት የሚገልጹ የጥበብ ስራዎች በብሔራዊ ትያትር ቀርበዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለብዙ ታሪክ፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ ታላቅ አገር ነች።

ብዝሃነት ፀጋችን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር፣ የሚደምርና የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ብዝሃነትን የጥንካሬ ምንጭ በማድረግ ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ እድገት እውን መሆን ማዋል አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ዳግመኛ ዓድዋ መሆኑን ገልጸው፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ በተግባር የታየው ህብረ-ብሔራዊነት በሌሎች የልማት ስራዎችም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም የህብረ ብሔራዊነት መገለጫዎችንና ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ላይ ሁሉም ዜጋ በሃላፊነት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባለብዙ ባህል፣ እሴትና ወግ ባለቤት አገር ነች ብለዋል።


 

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያኖሩት የጋራ እሴት ለህዝቦች ህብረ ብሔራዊነት መጎልበት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተለይም ባህላዊ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤  በዚህ ረገድ መንግስት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም