ቀጥታ፡

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ስርዓትን ማሻሻል ይገባል

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ስርዓትን ማሻሻል በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ትኩረት ሊደረግባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ቀዳሚው መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለፁ።  

ከነሐሴ 30 እስከ እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም ’’በሳይንስ፣ በገንዘብና በፍትሐዊ ሽግግር የአፍሪካን የአየር ንብረት እርምጃ ማንቃት” በሚል መሪ ሃሳብ  ሲካሄድ የቆየው 13ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥና ልማት ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ መርሃግብር ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ክላቨር ጋቴቴ እንዳሉት ጉባኤው የአፍሪካን ፍላጎት ከተግባር የሚያስተሳስር ድልድይ ነው።

ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤና በብራዚል በሚካሄደው ኮፕ-30 የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በአፍሪካ የአየር ንብረትን ተፅዕኖ ለመቋቋም በዓመት የሚያስፈልጋትን ፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ አፋጣኝና የተጠናከረ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደምትሻ ተናግረዋል።

በአፍሪካ የአየር ንብረትን የተመለከቱ አስፈላጊ መረጃና እውቀቶችን ለማግኘት ሀገር በቀል ጥበብን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አሰናስሎ መሄድ ይጠይቃል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ600 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ መሆናቸውን በማንሳት፥ ይህንን ለማስተካከል የአየር ንብረት ፋይናንስን ማሻሻል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ጀምስ ኪኒያንጂ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ቀናት የተካሄደው ጉባኤ ትርጉም ያለው ውይይት የተደረገበት ነው ብለዋል።


 

ባንኩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው በ2024 ብቻ ለአካታች የኃይል አቅርቦት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል።

አፍሪካ እስካሁን ካገኘችው የአየር ንብረት ፋይናንስ አብዛኛው በብድር መልክ የተገኘ ነው ያሉት ደግሞ  የፓን አፍሪካ አየር ንብረት ፍትህ ጥምረት የፖለቲካና ቴክኒክ ጉዳዮች ሊቀመንበር ኦገስቲን ጃምሺ ናቸው።


 

በተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ፅህፈት ቤት የአየር ንብረት አማካሪ ሊነስ ሞፈ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባኤው ጠንካራ መልዕክቶች የተላለፉበት እንደነበር አንስተዋል።


 

የዴቨሎፕመንት ትራንስፎርሜሽን የምርምር ተቋም መስራችና ኃላፊ ማርታ በቀለ በበኩላቸው ጉባኤው አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የራሷን መፍትሄ እንድታመላክት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም