ቀጥታ፡

በህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት በመገንባት ጠንካራ ሀገረ መንግስትን እውን ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን

ወላይታ ሶዶ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- በህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት በመገንባት ጠንካራ ሀገረ መንግስትን እውን ለማድረግ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ተገለፀ።

ጳጉሜን 2- የህብር ቀን በወላይታ ዞን እና በነቀምት ከተማ አስተዳደር "ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በወቅቱም የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ፤ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱና ብልጽግናን  የሚያረጋግጡ ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተለይም በለውጡ መንግስት የተገኙ ድሎችና ስኬቶች በግለሰብም ይሁን በጋራ የብልጽግናን ግብ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህም ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የወል ትርክት በመገንባት ሰላምንና አንድነትን ማጽናት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት ለመጣል የድርሻችንን መወጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ጠንካራ መንግስት ለመገንባት ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ያሳተፈ ሀገራዊና ህብረ-ብሔራዊ ማዕቀፍ መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም ናቸው።


 

መንግስት የኢትዮጵያውያን ብዝሃ ማንነትና አንድነት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲጓዙና ጠንካራ ሃገረ-መንግስትን እውን ለማድረግ እያደረገ ባለው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ህዝባችንን አስተባብረን እንተጋለን ብለዋል ።

ዕለቱም በዞኑና በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽንና ፓናል ውይይት የተከበረ ሲሆን የተለያዩ አካላትም ተሳትፈዋል።

በተመሳሳይም የህብር ቀን በነቀምቴ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል። 

በውይይቱ  ላይ የተገኙት የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ምስጋኑ ቱሉ ባደረጉት ንግግር በመተባበር አንድነታችንን ለማጠናከር በተሰራ ስራ ሀገርን ማስቀጠል መቻሉን ገልፀዋል። 


 

በዚህም የመደመር ፍልስፍና ውጤት በሆነው ህብረ-ብሔራዊነት የተገኙ ለውጦችን ለማጽናት የጀመርነውን የእድገት ጎዳናን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የደረስንበት የእድገት ደረጃ ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ እንጂ የሚያረካ ባለመሆኑም ይበልጥ መስራትና መተባበር ይገባናል ያሉት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ታደሰ ናቸው።

በብልፅግና ፓርቲ የነቀምቴ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ በየነ በበኩላቸው ሀገራችን በህብረ-ብሔራዊ ማንነት በጋራ በመቆም ባለፉት ዓመታት ሁለንተናዊ የዕድገት ውጤቶችን አስመዝግባለች ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም