ባንኩ በደብረ ብርሀን ከተማ ለ200 አቅመደካሞችና አረጋውያን ማእድ አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በደብረ ብርሀን ከተማ ለ200 አቅመደካሞችና አረጋውያን ማእድ አጋራ
ደብረብርሃን ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በደብረ ብርሀን ከተማ ለ200 አቅመደካሞችና አረጋውያን ማእድ አጋራ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት ባንኩ በሚሰጠው አገልግሎት በከተማው ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መፋጠን የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በዛሬው እለትም አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የፈጸመው ተግባር አርአያ መሆኑን ተናግረዋል።ባንኩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረብርሀን ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ጨበር እንደገለጹት ባንኩ ከመደበኛ ተግባሩ በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችም ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬም የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ 200 አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ግምት ያለው የማእድ ማጋራት አድርጓል ብለዋል።
በነፍስ ወከፍ የተደረገው ድጋፍ 25 ኪሎግራም የዳቦ ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይት፣ በጥሬ ገንዘብ 1 ሺህ 300 ብር እንዲሁም አንድ ደርዘን ደብተር ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑ መካከል አቶ ተክሌ ሞገስ እንዳሉት የተደረገላቸው ድጋፍ በአሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
ወይዘሮ በቀለች ደስታ በበኩላቸው በአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የተደረገልኝ ድጋፍ ከቤተሰቦቼ ጋር ተደስቼ ለማሳለፍ ያስችለኛል ብለዋል።