የህዳሴ ግድብ በርካታ አሉታዊ ቀንበሮችን የሰበረ የህዝባዊ ገድል ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ በርካታ አሉታዊ ቀንበሮችን የሰበረ የህዝባዊ ገድል ውጤት ነው
አርባ ምንጭ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ አሉታዊ ቀንበሮችን የሰበረ የህዝባዊ ገድል ውጤት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ የህዳሴ ሳምንት አክብሯል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከ60 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የታዳሽ ኃይል እንዲሁም ከ45 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅም ያላት ቢሆንም በአግባቡ ሳትጠቀም ቆይታለች።
ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም አቅማችን ተዳክሞ ቆይቷል የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በዚህ ቁጭት የተጀመረው የህዳሴ ግድብ በርካታ አሉታዊ ቀንበሮችን ሰባብሮ ለድል የበቃ ገድል ነው ብለዋል።
በተለያየ ሴራ ምክንያት ለዘመናት አባይን የመጠቀም መብት ሳይሳካ መቆየቱን ጠቁመው በመንግስት ቁርጠኛ አቋም ከጨለማ የመውጣት እና ከድህነት የመላቀቅ ጉዞ እውን መሆኑን ገልጸዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ስኬት ቁጭት የወለደው የአይበገሬነት ውጤት ነው።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለግድቡ ድጋፍ አለመስጠቱ የራሳችንን አቅም እንድንረዳ በማድረጉ በደረስንበት ስኬት ሳንዘናጋ የተሻለ እሳቤ ይዘን ወደፊት መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ የሁላችንም አሻራ ያረፈበት የኢትዮጵያውያን የጽናት ተምሳሌትና የድል አድራጊነት ምልክት ዳግም አድዋ ነው ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብደላ ከማል (ዶ/ር ) ናቸው።
ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑ ታምኖበት በተፈጠረው ጽናት ለፍፃሜ መድረሱ ተጨማሪ ሞራል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ በቀጠናው የኢትዮጵያን ተሰሚነት የሚያጎላ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩም የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።