ኢትዮጵያ የተጎናፀፈቻቸው ስኬቶች በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የተገኙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተጎናፀፈቻቸው ስኬቶች በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የተገኙ ናቸው
ገንዳ ውኃ፣ ደብረ ማርቆስና ደብረ ብርሃን ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የተጎናፀፈቻቸው ድሎችና ስኬቶች በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የተገኙ መሆናቸውን የህብር ቀን አከባበር ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
የህብር ቀን በገንዳ ውሃ፣ በደብረ ማርቆስና ደብረ ብርሃን ከተሞች "ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።
በምእራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ነዋሪ የሆኑት መላከሀይል ዘሚካኤል ሞገስ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የህብር መገለጫ የሆኑ የብዙ አኩሪ ድሎችና ባህሎች ባለቤት ናት።
የብዝሃ ብሔር፣ ሀይማኖትና ቋንቋ ባለቤት የሆነችው አገራችን ያገኘችውን ድል በማስጠበቅ በቀጣይ በህብርና በአንድነት ለሌላ ታሪክና ድል መዘጋጀትና መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
ሼክ ሙሀመድ ገደፋው በበኩላቸው ሀገሪቱ እስካሁን የተጎናፀፈቻቸው ስኬቶች በህብር የተፈፀሙ መሆናቸውን አንስተዋል።
የምእራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና የአስተዳዳሪው ተወካይ አቶ ደረሰ አዱኛ እንዳሉት ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነትን ለማረጋገጥ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት አስፈላጊ ነው።
በተያያዘ ዜና የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ተወካይ አቶ ባምላክ ታገለ እንደገለጹት የህብር ቀንን ስናስብ በአካባቢያችን ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ምህዳር በመፍጠር ነው።
ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነቷን አስከብራ የኖረችና በህብር ብዙ ስኬትና ውጤት እያስመዘገበች ዛሬ ላይ የደረሰች ታላቅ አገር ናት ብለዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ጌትነት ላዕለም እንዳሉት ህብርነት ወንድማማችነትን በማስፈን በሰላም አብሮ መኖርን የሚያረጋግጥ በመሆኑ በቀጣይም ለአንድነት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በደብረ ብርሃን ከተማ የህብር ቀን አከባበር ላይ እንዳሉት ህብር የኢትዮጵያ ህዝብ መገለጫ ነው።
የህብር ቀንን ስናከብር የመከባበር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህላችንን ለትውልድ በማስተማር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክለዮሀንስ ሀይለጊዮርጊስ፤ የህብር ቀንን ስናከብር አንድነታችንን አጠናክረን ለልማትና ሰላም ዘብ በመቆም ቃል ኪዳን በመግባት መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።
የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ በቀለች አሰፋ እንዳሉት የህብር ቀንን ስናከብር የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ዋዜማ ላይ መገኘታችን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።