ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያዊያን የመቻል እና የማንሰራራት ጅማሮ ብስራት ነው

ሆሳዕና፤  ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፦ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያዊያን የመቻልና የማንሰራራት ጅማሮ ብስራት ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላለፉት አመታት በዜጎች ጥሪትና ጉልበት ተገንብቶ ለስኬት የበቃበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን።

የህዳሴ ግድብ ከብርሃን ምንጭነቱም ባለፈ ኢትዮጵያዊያን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም መገንባት እንደሚችሉ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑም ይታወቃል። 

በመሆኑም የግድቡ ግንባታ ለስኬት መብቃቱ የኢትዮጵያዊያን የመቻልና የማንሰራራት ጅማሮ ብስራት መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አንተነህ ፈቃዱ ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ እምብርት ተነስቶ አገራትን አቆራርጦ የሚፈሰው የአባይ ወንዝ ለዘመናት ሲፈስ "የሀገር አድባር" እየተባለ ቢነገርለትም እስካሁን የሰጠው ጥቅም እንዳልነበረ ያነሳሉ።

ከብዙ ልፋትና ጥረት በኋላ ግን አባይ ተገርቶ የብርሃን ምንጭ፣ የዓሳ ሃብት መገኛ እና ለጉብኝት የሚመረጥ የመስህብ ስፍራ መሆን የቻለበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአካባቢው አገራት የልማት ትስስር መሰረት የጣለ፣ የኢትዮጵያዊያን የመቻል አቅም የተረጋገጠበትና የሀገር የማንሰራራት ብስራት መሆኑን አስረድተዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደትና ለመጣው ስኬት የኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሄራዊ አንድነትና በጽናት ለመጨረስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ሁሌም በታሪክ የሚታወስና ብዙ ሊነገርለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አቶ አንተነህ ገልጸዋል።

በክልሉ የቡታጅራ ነዋሪው አቶ ፍቃዱ አሶሬ እና  የሆሳዕና ከተማ  ነዋሪዋ ወይዘሮ ለምለም ማቲዎስ፤ የህዳሴ ግድብ በብዙ ልፋት፣ በገንዘብና ጉልበታችን ያሳካነው ፕሮጀክት በመሆኑ ለስኬት መብቃቱ የሁላችንም ደስታ ሆኗል ብለዋል።


 

የህዳሴ ግድብ ግንባታ በቀጣይ ለሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም እንደ ሀገር ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑን አንስተው በጋራ ከቆምን የማንሻገረው ችግርና የማናሳካው የልማት እቅድ እንደሌለ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም