የኢትዮጵያ የቡና ልማት በዘመናዊ አሰራሮች በመታገዝ እያስመዘገበ ያለውን እመርታ ለማጠናከር ይሰራል- ሚኒስትር አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቡና ልማት በዘመናዊ አሰራሮች በመታገዝ እያስመዘገበ ያለውን እመርታ ለማጠናከር ይሰራል- ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
ምዕራብ ጉጂ ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የቡና ልማት በተሰጠው ትኩረት ከልማዳዊ አሰራር ተላቆ በዘመናዊ አሰራሮች በማስደገፍ እየተመዘገበ ያለውን እመርታ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።
ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ቀርሳ ቀበሌ በቀርጫንሼ ግሩፕ በ750 ሄክታር መሬት ላይ በዘመናዊ መንገድ እየለማ ያለውን የቡና ማሳ ምልከታ አድርገዋል።
በወቅቱም ሚኒስትሩ እንዳሉት ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው።
በተለይም በዝርያ ማሻሻልና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እንዲሁም ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በማስተሳሰር ሽፋኑን ማስፋት በመቻሉ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ቡናና ከዘርፉ የሚገኝ ገቢ መጠን ማደጉን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የተጀመረውን ጥረት በማጠናከርና ከዘልማድ አሰራር በማላቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ ካደረግን ካለን አቅምና ሊለማ ከሚችል መሬት አንጻር የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የቀርጫንሼ ግሩፕ የቡና ልማት ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከር የቀርጫንሼ ግሩፕን ጨምሮ የግሉ ባለሀብት እያደረገው ያለውን ተሳትፎ የቡና ልማትን ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደሚቻል ተስፋን የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር የተሻሻለ የቡና ዝርያ ለማስፋፋት የሚያስችሉ ስራዎች እና ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂ ከሌሎች ሀገራት በመቅዳት ሀገራዊ የኤክስፖርት ገቢንና ዘርፉ ለስራ ዕድል ያለውን ሚና ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት አለም አቀፍ ተሳትፎና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አመራረትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማስደገፉ ስራ ወሳኝ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ናቸው።
የቀርጫንሼ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ እስራኤል ደገፋ (ዶ/ር) ቡናን ያለጥላ በመስኖ በማልማትና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ በዘላቂነት ከፍተኛ ምርት እንዲሰጥ የሚያስችሉ ሙከራዎችን በማድረግ ውጤታማ ሆነናል ብለዋል።
አዲስ ልምድ ቢሆንም በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት የሚሰጥ ዝርያ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በማሳው ቡናን የመትከልና መልቀም ሂደት በአጠቃላይ በሜካናይዝድ ማሽኖች እንደሚንቀሳቀስ ገልጸው ይህም ዘርፉን ውጤታማ አድርጓል ያሉት ዶክተር እስራኤል ልምዱ ከብራዚልና ከእስራኤል ሀገራት የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የቴስቲ ስፔሻሊቲ ቡና ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋይሰል አብዶና የካዮ ማውተን የቡና እርሻ ባለቤትና ማናጀር አቶ እስማኤል ሁሴን በበኩላቸው ቡናን በሜካናይዝድ ከጥላ ዛፍ ውጭ በመስኖ ማልማት እንደሚቻል ዕውቀት ቀስመናል ብለዋል።
'ቡናን በተለመደው ዘዴ ከማምረት በዘመናዊ መንገድ ማልማት ከተቻለ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል መመልከታቸውን ገልፀው ያዩትን ወደ ተግባር እንደሚለውጡም ተናግረዋል።
በመስክ ምልከታው ላይም የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡና ላኪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።