ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትውልዱ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነቱን ያደሰበት ዳግማዊ ዓድዋ ነው   

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዛሬ ትውልድ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነቱን ዳግም ያደሰበት ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳም ተስፋዬ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጳጉሜን 2 የሕብር ቀንን፤"ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።


 

በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳም ተስፋዬ እንዳሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዛሬ ትውልድ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነቱን ያደሰበት ዳግማዊ ዓድዋ ነው።

ግድቡ የህብርና የአንድነታችን ዓርማ፣ትውልድ ተሻጋሪ ሀብትና ቅርስ እንዲሁም የዲፕሎማሲያችን ውጤት የአብሮነታችን ስኬትና የይቻላል መንፈስ በተግባር የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን የሚያስተሳስሩን በርካታ እሴቶች ስላሉን በጋራ ከቆምን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት መመዝገቡን ገልጸው፤ በዚህ ዓመትም ለተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በህብረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በህብር የተሳሰሩ እና የተጋመዱ  ለረጅም ዓመታት አብረው በመቆም አገራቸውን በጋራ የገነቡ ናቸው ብለዋል።


 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የወል ትርክታችንና በህብረት ሆነን ያሳካነው ድል ነው ብለዋል። 


 

የህዳሴ ግድብ ታሪካዊና የአንድነት ውጤት እንዲሁም በህብረት ከሰራን የዕድገት ማማ ላይ መውጣት እንደምንችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ስኬት የዲፕሎማሲውን መዘውር የቀየር እና የኢትዮጵያን ስም ያደሰ መሆኑን በበዓሉ ላይ አወያይ የነበሩት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናግረዋል። 



 

ዳያስፖራው ለህዳሴው ግድብ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት በህብረት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መድረኮች የተለያዩ ድርድሮች ላይ በመሳተፍ ትልቅ ድል ማስመዝገቧን  የገለጹት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ውስብስብና አስቸጋሪ ሂደቶችን በማለፍ የግድቡ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በህብረት ሆነን በርካታ ነገሮችን አሳክተናል በቀጣይ ከዚህ በተሻለ መልኩ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም