በጉባዔው አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ድምጻቸውን በጋራ ያሰማሉ ለመፍትሔው እየሰሩ መሆኑንም ለዓለም ያሳያሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጉባዔው አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ድምጻቸውን በጋራ ያሰማሉ ለመፍትሔው እየሰሩ መሆኑንም ለዓለም ያሳያሉ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካውያን በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ለውጥ ጉባዔ ድምጻቸውን በጋራ ከማሰማት ባለፈ ለመፍትሔው በግንባር ቀደምነት እየሰሩ መሆኑን ለዓለም እንደሚያሳዩ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ "ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ነገ የሚጀመረውን ጉባኤ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ናት ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ እያገኘ አይደለም ብለዋል።
ነገ ከሚጀመረው ጉባዔ በፊት ቅድመ-ጉባዔዎቹ በተሳካ ሁኔታ መካሄዳቸውንና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች መነሳታቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን በጋራ መከላከል የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው በጽኑ ታምናለች ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከዚህ አኳያ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን አንስተዋል።
በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባዔ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ድምጻቸውን በጋራ ከማሰማት ባለፈ ለመፍትሔው እያከናወኗቸው የሚገኙ ሥራዎችን በተግባር የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ከአህጉራዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
ጉባዔው ማህበረሰብ ተኮር መፍትሄዎች ጎልተው የሚሰሙበት፣ የአፍሪካ የጋራ አጀንዳ የሚቀረጽበት እንዲሁም አገራት ለአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የማጣጣሚያ እቅድ እና ዘላቂ እድገት ቃል ኪዳኖችን የሚገቡበት ይሆናል ብለዋል።
በጉባዔው አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቁርጠኝነት የሚሰሩበት የአዲስ አበባ ድንጋጌ ስምምነት እንደሚጸድቅ ነው ያስታወቁት።
አፍሪካ በአየር ንብረት አስተዳደር ትክክለኛ ቦታ ለመያዝ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዙ ውሳኔዎች የተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ሚኒስትሯ ያነሱት።
በጉባዔው የተለያዩ አገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ25ሺ በላይ ተሳታፊዎች ይታደማሉ ብለዋል።
ከዋናው ጉባኤ ባለፈ ከ49 በላይ የጎንዮሽ ሁነቶች እንዲሁም መካነ ርዕዮች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።