ሰላምን በማጽናት የኢትዮጵያን ማንሠራራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና በጋራ ጥረታችን እናሸጋግራለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በማጽናት የኢትዮጵያን ማንሠራራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና በጋራ ጥረታችን እናሸጋግራለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2017(ኢዜአ)፦ሰላምን በማጽናት የኢትዮጵያን ማንሠራራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና በጋራ ጥረታችን እናሸጋግራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ "ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት" በሚል መሪ ሐሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ የጳጉሜን ቀናት አስቦ መዋል ዜጎች ለአዲስ ዓመት የግላቸውን መሻት እውን ለማድረግ ሲያቅዱ የመንግስት መነሳሳቶች፣ ዕቅድ እና አቅጣጫዎችን በዕቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጠናቀቅ ላይ ያለው ዓመት የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን መጠናቀቅ፣ የጋዝ ምርታችን ጫፍ መድረስ፣ ማዳበሪያ ለማምረት ስምምነት ማድረጋችን፣ የኮሪደር ልማት፣ የኢንዱስትሪዎች አምራችነትን ማጠናከር፣ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎችም ታላላቅ ስራዎች የተከናወኑበት ዓመት ነው ብለዋል፡፡
በመጭው ዓመት እነዚህን እመርታዎች አጠናክሮና አልቆ ለማስቀጠል ዋዜማ የሆኑትን የጳጉሜን ወር ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ማክበር ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ኅብራዊ ማንነቷን ተቀብሎና አስማምቶ የኖረ አንድነት እንዳላት ኢትዮጵያዊነት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንድ እጃችን የብልጽግና ጉዟችንን እያሳለጥን፤ በሌላ እጃችን ደግሞ ሰላማችንን በፅኑ መሰረት ላይ ማጽናት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ከሁለቱ አንዱ እጃችን ለአፍታም የሚደክም ከሆነ የምንፈልጋትን የበለጸገች ኢትዮጵያ የመገንባት የስኬት ጊዜ እንደሚራዘምም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የጸጥታ ሥራ እና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥራ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን አንስተው የጸጥታ አካላት የዴሞክራሲ ዘቦች፣ የማኅበራዊ ዋስትና ጠባቂዎች እና የኢኮኖሚያችን ኃይሎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና የፖለቲካ ዘርፍ የተሠማሩ አካላትም የሰላምና የደኅንነት ጠባቂዎችና አስጠባቂዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማንሠራራት መጀመሩን ጠቁመው ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች፤ የዘመናት ስብራቶቻችን እየተጠገኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የጸና ኢትዮጵያ በሁላችንም ልፋትና ትብብር እየተገነባች መሆኗን ጠቁመው በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በአይሲቲ ዘርፎች እመርታዎች እየመጡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በሁሉም ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች የመጣው ለውጥ ለሁሉም አስደማሚ ብቻ ሳይሆን ለማመንም የሚከብድ አዲስ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአንድ በኩል ሰላማችንን እያጸናን እንድንቀጥል በሌላ በኩል ደግሞ የብልጽግና ጉዟችንን ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንድንችል ማስጠበቅ፣ ማጽናት፣ ማሣለጥ እና ማቀናጀት ከአመራሩ የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ማስጠበቅ ከግጭት ጠንሳሾች፣ ከኮንትሮባንዲስቶች፣ ከኢኮኖሚ አሻጥረኞች፣ ከሕገ ወጥ የሰውና የገንዘብ አዘዋዋሪዎች፣ ከጽንፈኞች እና ከአሸባሪዎች የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ደኅንነት ሁሌም ማስጠብቅ ነው ብለዋል፡፡
ማጽናት ሲባል ደግሞ ያስጠበቅነው ሰላም ጸንቶ እንዲኖርና ሕዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ማሣለጥ የሰዎችና የሸቀጦች ዝውውር በሰላም እንዲቀላጠፍ፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ያለ እንከን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሣለጡ ማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማቀናጀት ማለት ደግሞ ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተማዎች፣ ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው ለሰላምና ለጸጥታ ተግባር እንደ አንድ አካል ሆነው መሥራት መቻል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡