ቀጥታ፡

አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ልማታችንን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን

ደሴና ወልድያ ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ልማታችንና ሉዓላዊነታችንን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

"ብዝኀነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ጳጉሜን 2 የህብር ቀን በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች በደሴና ወልዲያ ከተሞች ታስቦ ውሏል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና የከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ኮማንደር ሰዒድ አሊ እንደገለፁት፣ ህብር የአንድነታችን መገለጫ፣ የድሎቻችንና የሰላማችን መሠረት ነው።

ኢትዮጵያ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነትና ሌሎች ሃብቶች ባለቤት በመሆኗ ብዝኃነታችን ውበትና ጌጣችን መሆኑን ለአለም ህዝብ ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል። 

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ አቶ አሰፋ የሱፍ በበኩላቸው አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ልማታችንና ሉዓላዊነታችንን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።


 

ህብር ኃይላችን፣ ጥንካሬያችን፣ ጉልበታችንንና የድላችን መሠረት በመሆኑ በህብር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ራህመት አየለ በበኩላቸው ብዝኃነታችን ውበትና ጌጣችን በመሆኑ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ሉዓላዊነታችን፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ እንሰራለን ብለዋል።

ዕለቱን አስመልክቶም ከ150 ለሚበልጡ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

በተያያዘ ዜና የወልዲያ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሞገስ ሞላ የህብር ቀን በወልድያ ከተማ ሲከበር እንደገለጹት ብዝሃነትን ጠብቆ በአገር ሰላምና ልማት ላይ በአንድነት መቆም ቁልፍ ስራ  ነው። 

ኢትዮጵያውያን በበርካታ የወል ታሪኮች፣ በአብሮነት እሴቶችና በባህሎቻችን ምሳሌ ሆነን መቆየታችንን ለሌላው አለም በማሳወቅና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ መስራት አለብን ብለዋል። 

በእለቱም የህብር መገለጫ በሆነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰበሰበ ዱቄት፣ ሽሮ፣ በርበሬና አልባሳት ለ396  በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች ድጋፍ መደረጉ ተመልክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም