ቀጥታ፡

በብዝሃነት የተሳሰረ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን-ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) 

ጋምቤላ ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- በደመቀ ብዝሃነት የተሳሰረ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለጹ።

ጳጉሜን 2 የኅብር ቀን ’’ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥና ዐቅም ነው’’ በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዕለቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን ባላቸው የደመቀ ብዝሃነትና በደም የተሳሰረ አንድነት ታሪካቸውን አጽንተው ቆይተዋል ብለዋል።

በብዝሃነት ውስጥ ያለው ህብረ ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት ኢትዮጵያውያን የሚያጋጥማቸውን ፈተና ሁሉ በድል አድራጊነት እንዲሻገሩ ጽናት ሆኗቸው ቆይቷል ሲሉም  ተናግረዋል።

በመሆኑም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህረሰብ በመገንባት የክልሉን ብሎም የሀገርን እድገትና ብልጽግናን ለማፋጠን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።


 

በተለይም "ብዝሃነት ለእኛ ለኢትዮጵያውን የአንድነታችንና የአብሮነታችን ጌጥ ነው" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህን እሴት የዘመኑ ትውልድ በመጠበቅ ለሀገሩ እድገትና ብልጽግና ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዘንድሮው የጳጉሜን 2 ’’የኅብር ቀን’’ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜ በተበሰረበት ወቅት መከበሩ ልዩ ትርጉም ያሰጠዋል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

"ብዝሃነታችን የጠንካራ ማንነታችን ታሪክ መሰረት ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ ናቸው።


 

እናም በብዝሃነት ውስጥ ያለውን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር የተጀመረውን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ዳር ለማድረስ እኛ የዘመኑ ትወልድ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ጳጉሜን 2 የኅብር ቀን በክልሉ ’’ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥና ዐቅም ነው’’ በሚል መሪ ሀሳብ በስፖርታዊ እንቅስቃሴና በፓናል ውይይት ተክብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም