የሀገራችንን ብዝኃነት፣ ውበትና ኅብረ ብሔራዊነትን በአንድነት አጎልቶ ለማሳየትና ለማጽናት የኅብር ቀንን ማክበር ወሳኝነት አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራችንን ብዝኃነት፣ ውበትና ኅብረ ብሔራዊነትን በአንድነት አጎልቶ ለማሳየትና ለማጽናት የኅብር ቀንን ማክበር ወሳኝነት አለው
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-የሀገራችንን ብዝኃነት፣ ውበትና ኅብረ ብሔራዊነትን በአንድነት አጎልቶ ለማሳየትና ለማጽናት የኅብር ቀንን ማክበር ወሳኝነት እንዳለው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
ጳጉሜን 2 "የኅብር ቀን" በሚል ስያሜ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዕለቱን "ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የብዝኃነታችን መገለጫና ነጸብራቅ የሆኑ፣ የሚያስተሳስሩ የበርካታ ባህል፣ ታሪክ፣ የተፈጥሮ ፀጋና መልክአ ምድር ባለቤት ናት፡፡
ቀደምት አባቶች በጋራ ጀግንነት ዳር ድንበሯን በማስከበር ሰንደቃችንን ከዓድዋ ተራሮች በላይ በማውለብለብ ለዓለም የነፃነት ትግል ቀንዲል የሆኑባትና ለዘመናት የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት ተምሳሌትም ናት በማለት ገልጸዋል፡፡
ከትናንት የወረስናቸው መልካም እሴቶቻችንን በማጠናከርና እንደ ህዳሴ እና አረንጓዴ አሻራ ያሉ አዳዲስ ድሎችን በቀጣይነት ለማስመዝገብ ኀብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጽናትና የወል ትርክታችንን ማጉላት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የሀገራችንን ብዝኃነት፣ ውበትና ኅብረ ብሔራዊነት በአንድነት አጎልቶ ለማሳየትና ለማጽናት የኅብር ቀንን ማክበር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
በሀገራችን የጋራ ጥረት የሚጠይቁና ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ትልሞች መኖራቸው አንስተው፤ እነዚህን ትልሞች እውን ማድረግ የሚቻለው ኅብረ - ብሔራዊ አንድነታችን በማጠናከር ነው ብለዋል፡፡
የጳጉሜን ወር ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የ13 ወር ፀጋ ባለቤት እንዳደረጋት ጠቅሰው፤ ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በየዓመቱ የጳጉሜ ቀናት በልዩ ልዩ ሁነቶች እያከበረ ነው ብለዋል ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕለቱን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ለተቋሙ ሰራተኞችና ለሌሎች የህብረሰብ ክፍሎች ለበዓል ማሳለፊያ እገዛ በማድረግ አሳልፎታል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሲሳይ አላዩ እና ወይዘሮ ነጻነት እምሩ የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን ያለ ምንም ችግር በደስታ እንዲያሳልፉ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል ፡፡ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡