ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ህብር ውጤት ነው 

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያዊያን የስራና የህብረት ውጤት ነው ሲሉ ኢዜአ በአዲስ አበባ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያዊያን ገንዘብ፣ የላብ አሻራ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊመረቅ ቀናት ቀርተውታል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የግድቡ እውን መሆን በውስጣቸው የፈጠረባቸውን ደስታ ለኢዜአ አጋርተዋል።

አርቲስት ሰለሞን ታሼ (ጋጋ) አባይን ለሀገራዊ ጥቅም ማዋል አለመቻላችን በተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች ለዘመናት በቁጭት ሲገለጽ እንደነበረ ያወሳል።

አሁን ላይ ይህ ታሪክ ተቀይሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተባበረ ክንድ ሰርተን ማጠናቀቅ መቻላችን የሚያኮራ ተግባር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የደረሱባትን አለም አቀፍ ጫናዎቸ ተቋቁማ ግድቡን እውን ማድረጓ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ንግስት ቅጥላ ናቸው።


 

የመዲናዋ ነዋሪ አቶ እሸቱ አለሙ  በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያንን በህብር ያስተሳሰረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለዚህ ቀን በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

አቶ ሲሳይ ከበደ በተመሳሳይ የህዳሴው ግድብ መሳካት እንደ ሀገር ለምንሰራቸው የልማት ስራዎች ሰፊ መነሳሳትን የሚፈጥር  መሆኑን ተናግረዋል።


 

አርቲስት ሰለሞን በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሙያችን ህዝብንና ሀገርን ማገልገላችንን አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል ብሏል። 

ወይዘሮ ንግስት ቅጥላ ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ያለውን አቅም አሟጦ እንዲጠቀም ጠይቀዋል።

ህዳሴ ግድብን በመሰሉና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚሰሩ የተለያዩ ስራዎች ላይ ከመሳተፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ አቶ እሸቱ  አለሙ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም