ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የታየው ህብረትና አንድነት ለሁለተናዊ ዕድገት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ላይ የታየው ህብረትና አንድነት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ በሚከናወኑ ተግባራት ላይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የብሄራዊ ቡድን አትሌቲክስ አሰልጣኞች እና አትሌቶች ገለጹ። 

ኢትዮጵያውያን ያለማንም እርዳታ በተባበረ ክንድ እውን ያደረጉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብና ደም፣ ከዜጎች በተሰበሰብ አገራዊ አንጡራ ሃብት ለፍጻሜ መብቃቱ ለአፍሪካውያን ትልቅ የታሪክ እጥፋት የፈጠረና የኩራት ምንጭ ለመሆን የበቃ ነው፡፡

ኤዚአ ያነጋገራቸው የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አትሌቶች እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጁ መሆኑ ትልቅ ደስታ ፈጥሮላቸዋል፡፡

የሶስት ሺህ መሰናክል ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ንጉሴ ጊቻሞ (ዶ/ር )እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ያለማንም ድጋፍ በራሷ አቅም ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቋ የሚያስደንቅ ነው፡፡ 


 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ዘመናት ላስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን የመልማትና የማደግ ቁጭት ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

የረጅም ርቀት አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ በበኩላቸው፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የህዳሴ ግድብ ፍሬ አፍርቶ ማየት የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል፡።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ  የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን ማብሰሪያ እንደሆነም ተናግረዋል።

አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅማሮው አንስቶ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አሰልጣኝ ሃጂ አዴሎ፤ በሌሎች የልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል።


 

ይህንን ታሪክ የሰራው ትውልድ አካል በመሆኑ እድለኛ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል  አትሌት አብርሃም ስሜ ነው፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዓድዋ መሆኑን አንስቶ፤ የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ ለመቀየር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስታውቋል፡፡ 


 

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጣው የብሄራዊ ቡድኑ የስምንት መቶ ርቀት አትሌት ዮሐንስ ተፈራ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሰሩት ግድብ መጠናቀቁ በቃላት መግለጽ የማይቻል ልዩ ስሜት የሚፈጥር  ነው ብሏል።

አሰልጣኞቹ እና አትሌቶቹ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የትኛውንም ፕሮጀክት ማሳካት እንደምትችል በተግባራ ያሳየችበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


 

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የታየው ህብረትና አንድነት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም