ቀጥታ፡

የህብር ቀን መከበሩ አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ያግዛል

ሐረር፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-  ጳጉሜን 2 የህብር ቀን  መከበሩ በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲጎለብቱና አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ያግዛል ሲሉ የሐረሪ ክልል  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ገለጹ።

ጳጉሜ 2 የህብር ቀን በመላ ሀገሪቷ በተለያዩ ሁነቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

ዕለቱ በሐረሪ ክልልም ህሙማንን በመጠየቅ እና በሌሎች የተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።


 

ቀኑን በማስመልከት  የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የእግር ጉዞ አከናውነዋል።

እንዲሁም በከተማው በሚገኘው ጀጉላ ጠቅላላ ሆስፒታል ህሙማንን የመጠየቅ መርሃግብር የተካሄደ ሲሆን ጎን ለጎን የንፅህና መጠበቂያና የምግብ ስጦታም ተበርክቷል።

በተጨማሪም ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ ማዕድ የማጋራትና ሌሎች መርሃ ግብሮችም ተከናውነዋል።

"ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥና ዐቅም ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ቀኑ በአሚር አብዱላሂ የመሰብሰቢያ አዳራሽም  በፓናል ውይይት በመከበር ላይ ይገኛል።


 

በዚሁ ወቅት  የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እንዳሉት ቀኑ በህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነትና የአንድነት እሴት ይበልጥ ለማጠናከር  ያግዛል።

የህብር ቀን ህብረ ብሔራዊነትን ከማጎልበት ባለፈ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።

እንዲሁም  የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና  አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑም የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም