በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል አውድ ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል አውድ ተፈጥሯል
አሶሳ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል አውድ መፈጠሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ተናገሩ።
ጳጉሜን 2 የህብር ቀን "ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥና ዐቅም ነው" በሚል መሪ ሐሳብ በአሶሳ ከተማ በፓናል ውይይት እንዲሁም በከተማዋ የተገነቡ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ መነሻ የውይይት ጽሁፍ ያቀረቡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ እንደተናገሩት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ሆነ በመላ ኢትዮጵያ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ አውድ ተፈጥሯል።
ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥና ዐቅም የሆነበት በርካታ ማሳያዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ በተለይም ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በአንድነት በመቆም የድል ባለቤት መሆናቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
ህብረ ብሔራዊነትን የሚያፀና የወል ትርክት ግንባታ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ህብር የበለጠ እንዲጠናከር እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በህብር ያሳካናቸው ክልላዊ እና ሀገራዊ ድሎችን ለማስቀጠል አሁንም በጋራ መቆምና የሀገርን ከፍታ የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የብዝሃነት መገለጫ በሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱም የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።