ብዝኃነት ዐቅም፣ ውበት እና ጌጥ ነው”- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ብዝኃነት ዐቅም፣ ውበት እና ጌጥ ነው”- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 2/2017(ኢዜአ)፦"“ብዝኃነት ዐቅም፣ውበት እና ጌጥ ነው፤ በዚያው ልክ ልንጠቀምበት ይገባል” ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ አስገነዘቡ፡፡
“ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ መልእክት የኅብር ቀን በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተከብሯል፡፡
በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ ብዝኃነት የተሰናሰነ ዐቅም መኾኑን በመረዳት የማንነት፣ የሐሳብ፣ የታሪክ፣ የባህል እና የመሳሰሉትን ብዝኃነቶች የሚያስተናግድ ሥርዐት እየዳበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ብዝኃነት የልዩ ልዩ መገለጫዎች ስብጥር ውጤት በመኾኑ የላቀ ዐቅም እና ውበት የሚፈጥር ጌጥ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
''ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ'' በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የፌዴራል ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ተወካይ ኃላፊ እንዳለው ሙሉዓለም ደግሞ የብዝኃነትን ዐቅም በሰንበሌጥ ወክለው አቅርበዋል፡፡
ሰንበሌጥ ብቻውን ነፋስ፣ ፀሐይ እና ዝናብ እንደማይቋቋም ያስታወሱት አቶ እንዳለው “ሰብሰብ ሲል ግን ጥንካሬን በመጋራት ቤትን ያህል መሠረታዊ መጠለያ ይገነባል፤ የቤት ክዳን በመኾን ከዝናብ እና ፀሐይ ይከላከላል፤ ቤቱንም ማራኪ ዕይታ ይሰጠዋል፡፡
ብዝኃነትም እንዲሁ ነው፤ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ማንነት፣ አንድ አመለካከት ብቻውን ውበትም ዐቅምም ያንሰዋል፤ በርካቶች ሲሰናሰኑ ግን ዐቅምም ውበትም ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡
የኅብር ቀንን በፓናል ውይይት ያከበረው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለኾኑ ሠራተኞችም ማዕድ አጋርቷል፡፡