በክልሉ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥኑ የለውጡ መንግስት ድሎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥኑ የለውጡ መንግስት ድሎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሀዋሳ ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በለውጡ መንግስት የተገኙና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥኑ ድሎችን የማስቀጠል ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገለጹ።
''የህብር ቀን'' በክልል ደረጃ በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትዕይንቶች ተከብሯል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር በለውጡ መንግስት የተገኙ ድሎችን ማስቀጠል ይገባል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሀገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው የሀገራችን የከፍታ፣ የህዝቦች የትስስርና ህብረ-ብሔራዊ ቀለም መገለጫ ምልክት የሆነው የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ለዚህ አብነት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ህዳሴ የአንድነት ውጤትና ስንደመር የምናምር፣ ስንተባበር የምንከብር፣ የአይበገሬ ማንነታችን ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስትም በሀገራዊ እሳቤ የተቃኘ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል።
የጋራ ትርክትን በመገንባት ክልሉን የሰላምና የልማት ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥኑ ድሎችን የማስቀጠል ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው ብዝሃ ማንነት ለጋራ ስነ ልቦናና አንድነት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
''የለውጡ መንግስት የመደመር እሳቤ የጥላቻን ድልድይ በመስበር በአንድነት ለልማትና ለሰላም የምንሰራበትን ምቹ እድል ፈጥሯል'' ብለዋል።
በክልሉና የብዝሃነት ምሳሌ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ ስራዎችም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ አመላካች በመሆናቸው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎችና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።