ከካርበን ግብይት ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬት እና የደን አሥተዳደር ልምዶችን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከካርበን ግብይት ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬት እና የደን አሥተዳደር ልምዶችን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017 (ኢዜአ)፡- ከካርበን ግብይት ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬት እና የደን አሥተዳደር ልምዶችን የማሳደግ ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች እና ስልቶች ውስጥ በመሳተፍ በካርበን ገበያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ሀብት ጥናት መሪ ሥራ አስፈጸሚ ብሥራት ኃይለሚካኤል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት እና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈች እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ የደን ልማትን፣ የደን መልሶ ማልማት እና ዘላቂ የመሬት አያያዝን ጭምር እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎም ካርበንን ከአየር ላይ የማስወገድ እና በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ መንገድ እንዲከማች አስተዋፅኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ፓሪስ ስምምነት ባሉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች እና ስልቶች ውስጥ በመሳተፍ በካርበን ገበያ የመሰማራት ፍላጎትን ማሳየቷንም አውስተዋል።
በኪዮቶ ፕሮቶኮል መሰረት እንደ ንፁህ ልማት ሜካኒዝም (CDM) የካርበን ግብይት ማዕቀፎችን በማዘጋጀት በካርበን ገበያዎች ላይ ለመሳተፍ ስትሠራ መቆየቷንም አስረድተዋል።
ሀገራችን የካርበን ክሬዲት የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገች ነው ያሉት አቶ ብሥራት፤ ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ሊሸጥ ይችላል ነው ያሉት።
ወደ ካርበን ገበያ ለመግባትም ኢትዮጵያ፤ የካርበን ገበያ ተሳትፎን ለመደገፍ ብሔራዊ ፖሊሲዎችን እና ደንቦችን የማዘጋጀት፣ልቀቶችን እና የካርበን ክሬዲቶችን ለመለካት፣ ሪፖርት ለማድረግ እና ለማረጋገጥ (MRV) ተቋማትን እያቋቋመች እና ማዕቀፎችንም እያሰናዳች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የካርበን ክሬዲቶችን ለማምረት እና ለመሸጥ በዓለም አቀፍ አጋርነት እና ፕሮጀክቶች ውስጥ መሳተፍ፣ ከካርበን ግብይት ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬት እና የደን አሥተዳደር ልምዶችን የማሳደግ ተግባራትን እያከናወነች ነው ብለዋል።
በካርበን ንግድ ላይ በንቃት ለመሳተፍ በፖሊሲዎች፣ በፕሮጀክቶች እና በዓለም አቀፍ ትብብር፤ ደኖችን እና ዘላቂ የመሬት አጠቃቀምን በማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለማስተካከል እና ለመቀነስ እየተጋች መሆኗንም አመላክተዋል።
ለደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ ከፍ ያለ እንክብካቤ የሚያደርጉ ሀገራት በካርበን ሽያጭ ገቢ እንደሚያገኙም አስገንዝበዋል።
የካርበን ግብይት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በገበያ ላይ የተመሰረተ አካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ የካርቦን ክሬዲቶችን መግዛት እና መሸጥን ያካትታል ብለዋል።
አንድ ክሬዲት አንድ ሜትሪክ ቶን የካርበን ዳይኦክሳይድ ወይም ተመጣጣኝ ጋዞችን መቀነስ ወይም መወገድን የሚወክል መሆኑንም አስረድተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በካርበን ግብይት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በአጽንኦት ምክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል።