ቀጥታ፡

ጉባኤዎቹ ያለምን የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲካሄዱ ዝግጅት ተደርጓል-የፌደራል ፖሊስ

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ጉባኤዎች ያለምን የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲካሄዱ ለማድረግ ከጉባኤዎቹ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ እስከ ፊፃሜ ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰው ኃይል ስምሪት መደረጉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ጨምሮ የአፍሪካ-ካሪቢያን መሪዎች ጉባኤ እና በቀጣይም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ጉባኤዎቹ ያለምን የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲካሄዱ ለማድረግ ከጉባኤዎቹ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ እስከ ፊፃሜ ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰው ኃይል ስምሪት አድርጓል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ በርካታ የትራፊክ ፖሊሶችም ስምሪት ወስደው የትራፊክ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርጉ እየገለፀ መንገዶች እንዳይጨናነቁ ኅብረተሰቡም የድርሻውን እንዲወጣ ይጠይቃል።

ኅብረተሰቡ እስከአሁን እያሳየ ላለው ድጋፍ ምስጋውን እያቀረበ በቀጣይ ለሚኖሩ አጠቃላይ የፀጥታና የትራፊክ ደንብ ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም