ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ ለአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራ ምሳሌ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ ለአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎች መከላከል እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ስራ ምሳሌ የሚሆን ስራ ነው ሲሉ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ ገለጹ።

ፋራይ ዚሙድዚ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የዛፎች እና የሌሎች ተፈጥሮ ሀብቶች እንክብካቤ እና አስተዳደር ለቀጣይ ትውልዶች የሚጠቅም ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ መንግስት ዛፎችን በመትከል እና በመንከባከብ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ስራ እና የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል ዜጎች ከመብላት ባለፈ ምርቱን በመሸጥ ገቢ ማግኘቱ አበረታች እንደሆነ ተናግረዋል።

አረንጓዴ አሻራ አፈርን በመጠበቅ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

ተወካዩ የአፈርና ውሃ ሀብቶች ጥበቃ እንዲሁም በርካታ ችግኞችን መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ፋኦ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እንደሚደግፍ አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ እንዳይከሰት ማድረግ ላይ በትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአፍሪካ የልማት ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥን መከላከልን ያማከሉ መሆን አለባቸው ያሉት ዚሙድዚ ለዚህም ሀገራት ከተበጣጠሰ ጥረት ይልቅ የተቀናጀ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን የሚከላከሉ ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄዎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሌሎችን ከመጠበቅ ይልቅ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን መተግበር እና እርስ በእርስ መማማር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

አረንጓዴ አሻራ ለአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራ ምሳሌ የሚሆን ኢኒሼቲቭ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በተሞክሮነት እንደምታቀርብ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም