ቀጥታ፡

የአትሌቲክስ ቡድኑ የኢትዮጵያን ማንሰራራት ጉዞ ለዓለም የማሳየት ድርብ ሃላፊነት ተጥሎበታል- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፦ በ20ኛው የጃፓን ቶክዮ የዓለም አትሌቲክስ  ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው  የኢትዮጵያ  አትሌቲክስ  ቡድን የኢትዮጵያን  ማንሰራራት ጉዞ ለዓለም  የማሳየት ድርብ ሃላፊነት ተጥሎበታል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ሸዊት ሻንካ ገለጹ።  

በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለሚሳተፈው የአትሌቲክስ ልዑክ አሸኛኘት ተደርጎለታል።  

በመርሃግብሩ  ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የመንግሥት  የስራ ሃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ  የጃፓን  አምባሳደር  ሺባታ  ሂሮኖሪኝ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህንን ጨምሮ የስፖርት ቤተሰብ አባላት ተግኝተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በጃፓን የሚካሄደው ውድድር ድል ከማስመዝገብ ባለፈ የኢትዮጵያን ማንሰራራት ለዓለም የምናሳይበት ነው። 

ከዚህ አኳያ የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያን ለውጥ እና የማንሰራራት ጉዞ ለዓለም የማሳየት ድርብ ሃላፊነት እደተጣለበት አመልክተዋል። 

ስፖርት ለአገራት ትስስር ዲፕሎማሲ መጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ ውድድሩ መሰል ዓላማዎችን ለማሳከት ዓይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አትሌቲክሱን ለማጠናከር ከአቅም ግንባታ ስልጠና  ተደራሽ ከማድረግ  ባለፈ  የመሮጫ ትራክ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው ብለዋል። 

ስታዲየሞችን ጨምሮ  ስፖርት ማዘውተሪያ ስፈራዎች ግንባታ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ  በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አትሌቶች ሁልጊዜም ድል በማድረግ ኢትዮጵያዊያን አንገታችንን ቀና እያደረጉን ነው ብለዋል።

ዛሬ የተሸኛቹ አትሌቶች እንደ ቀደሙት ጀግኖች አትሌቶች  የኢትዮጵያ ኩራት እንድትሆኑ አደራ አለባችሁ ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ በጃፓን ቶክዮ ኢትዮጵያን የሚወከሉ አትሌቶች ጥሩ ዝግጅ ማድረጋቸውን ነው የገለፀው።

የተሻለ  ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደርጋለን ሲልም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም