ቀጥታ፡

መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚያከናውኑትን ተግባር ማጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017 (ኢዜአ)፡- መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚያከናውኑትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለጸ።

መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት አካታች ኮሚቴ ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በመሪዎች ስብሰባ ወቅት የሚያቀርቡትን ጥያቄና መልዕክት በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት አካታች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮናስ ገብሩ መረሃ-ግብሩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኮሚቴው ላለፉት ወራት በጋራ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ተከታታይ ውይይቶችን በበይነ መረብ ሲያካሒድ ቆይቷል።

ኮሚቴው በ16 ቡድን የተከፈለ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ዘርፍ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በአፍሪካ ደረጃ ሲከናውኑ የቆዩትን ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በሚመለከት በመሪዎች ጉባኤ ላይ ጥያቄና መልዕክት እንዲያቀርብ እድል መመቻቸቱን ነው የጠቀሱት።

ዛሬ የተደረገው የገጽ ለገጽ ውይይት የዚሁ አካል መሆኑን አመልክተው፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተከትሎ ጥያቄዎቻቸው ላይ የተደረገ ምክክር መሆኑን ተናግረዋል።

ጥያቄዎቹና መልዕክቶቹ ሰኞ በሚጀምረው የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚቀርቡ ገልጸው፤ ይህም በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ምላሽ ለማስጠት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ጥያቄና መልዕክቶቹ 16ቱም ቡድኖች ለወከሏቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድምጽ ለመሆን፤ እድል የሚፈጥር ስለመሆኑም አብራርተዋል።

እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መንስኤ የሆኑ አካላትና አገራት ሁኔታውን እንዲረዱና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የሚያከናውኑትን ቅንጅታዊ አሰራር እንዲያጠናክሩ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም