ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ ለ2ሺህ 900 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ ለ2ሺህ 900 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
ሰመራ/ድሬዳዋ ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማ እና ድሬዳዋ አስተዳደር ለ2ሺህ 900 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምሰራቅ ምስራቅ ሪጅን ዳይሬክተር ፍፁም ብርሃነ በዱብቲ ከተማ ድጋፍ ባረጉበት ወቅት እንዳሉት፤ "በጎነት " በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮ ቴሌኮም በመላ አገሪቱ የተለያዮ ድጋፎችን እያደረገ ነው።
በዱብቲ ከተማ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ለሆኑ ለ1ሺህ 500 ተማሪዎች ደብተርና እስክሪብቶ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በትናንትናው ዕለት ለሠላምና ዕድርና መረዳጃ ማህበር 875 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ መስጠታቸውን አውስተዋል።
ይህ ድጋፍ ማህበራዊ ኀላፊነትን መወጣትና የመተባበር እሴታችን አካል ነው ብለዋል።
በዕለቱ የተገኙት የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም ያደረገው ድጋፍ አጋርነቱን ከፍ በማድረግ ያሳየበት ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መጪውን አዲስ ዓመት በማስመልከት ኢትዮ-ቴሌኮምና እና ንግድ ባንክ በድሬደዋ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።
በዚህም የኢትዮ ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን ለ1ሺህ200 ተማሪዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት ለ200 ተማሪዎች ደብተርና ስክሪፕቶ ማበርከታቸው ተመልክቷል።
ድጋፉን ለድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ያስረከቡት የኢትዮ ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጣሰው ሽመልስ በወቅቱ እንዳሉት ፤ ለችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ የሁሉም ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል ።
ኢትዮ ቴሌኮም በአስተዳደሩና በምስራቅ ሪጅን በሚገኙ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ማህበራዊ ችግሮች እንዲቃለሉ በየዓመቱ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በመተባበርና በመቀናጀት የትኛውንም ማህበራዊ ችግሮች በራስ አቅም መፍታት እንችላለን ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ የድሬዳዋ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ በቃና ናቸው።
ድጋፉን የተቀበሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።