የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት ሁነኛ መሰረት የሚያኖር ነው- ኡስታዝ ጀማል በሽር - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት ሁነኛ መሰረት የሚያኖር ነው- ኡስታዝ ጀማል በሽር

ድሬዳዋ፣ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ) ፡- የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት ሁነኛ መሰረት የሚያኖር መሆኑን "የዓባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር ተናገሩ።
የጽናት ቀን "ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ "የዓባይ ንጉሶች” ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት መሐመድ አል አሩሲ ተገኝተዋል።
ኡስታዝ ጀማል በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የህዳሴ ግድብ ማንንም በማይጎዳ መልኩ በትብብር መልማትን መሰረት አድርጎ በራስ ሃብት ተመስርቶ የተገነባ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለቀጣናው አገራት የጋራ ተጠቃሚነትንና የልማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለኢትዮጵያ ደግሞ እድገቷ ጽኑ መሰረት የሚያስይዝ ሁነኛ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እውነታዎችን በማሳየት በመከራከር የሚታወቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ፤ የግድቡ ግንባታ ስኬት የመላ ኢትዮጵያዊያን ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያዊያን ጥሪትና ጉልበት የተገነባ ከሀገርም አልፎ ለሌሎች ብርሃን መስጠት የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ ለስኬቱ የሁላችንም ደስታ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን እድገት ለማስቀጠል በግድቡ ግንባታ የታየው የህዝብ ትብብርና አንድነት እንዲሁም ለችግሮች የማይበገር ጽናታችን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።