ቀጥታ፡

‎በፅናትና በአንድነት ቆመን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን

ባሕርዳር፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፡- በፅናትና በአንድነት ቆመን  ተግተን በመስራት ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን   ሲሉ  የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ   ጎሹ እንዳላማው ተናገሩ። 

‎"ፅኑ መሰረት ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን  የፅናት ቀን በባሕርዳር   ከተማ በተለያየ ዝግጀት ተከብሯል። 


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ፤ የክልሉንም ሆነ የኢትዮጵያን ክብርና ገናናነት ከፍ ለማድረግ ጠንክረን  በመስራት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

‎የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የፀጥታ አካላት  በከፈሉት መስዋዕትነት በአካባቢው  ሰላምን ማሰፈን መቻሉን ገልጸዋል። 

‎ሰላምን በማፅናትና ልማቱን የማፋጠን ተግባር ዛሬም እንደትላንቱ   ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

‎የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት አናጋው በበኩላቸው፤ የከተማውን ሰላም አፅንቶ ‎   በማስቀጠል የሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰላምን  በዘላቂነት በማስከበር እየተከናወነ  ያለውን ልማት ለማፋጠን መስዋዕትነት ተከፍሏል   ያሉት ደግሞ የከተማው  አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ናቸው።

‎ዕለቱም ‎በዓላማቸው ፀንተው በመቆም መስዋዕትነት የከፈሉ ጓዶችን የምንዘክርበት ነው፤ ይህም ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ጠንክረን ለመስራት ይበልጥ ያነሳሳናል ብለዋል።

‎በመከላከያ ሰራዊት የኮማንዶ አየር ወለድ አባል   አስር አለቃ ደምረው አበበ በሰጡት አስተያየት፤ ጀግኖች አባቶቻችን በፅናት ያቆየዋትን ሀገር እኛም ፅናትን ተላብሰን  እናስቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ 

በመረሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ አድማ ብተና እና መደበኛ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተስብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም