በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የህዝቡ ድጋፍና ሰራዊቱ ጠንካራ የሀገር መከታ መሆኑ ለስኬት አብቅቶታል- የሰራዊቱ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የህዝቡ ድጋፍና ሰራዊቱ ጠንካራ የሀገር መከታ መሆኑ ለስኬት አብቅቶታል- የሰራዊቱ አባላት
ባሕርዳር፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የመንግስት ቁርጠኝነት፣ የህዝቡ ድጋፍና ሰራዊቱ ጠንካራ የሀገር መከታ መሆኑ ለስኬት አብቅቶታል ሲሉ የሰራዊቱ አባላት ተናገሩ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለፍተውና ደክመው ለስኬት እንዲበቃ አድርገዋል።
የግድቡ ግንባታ ሂደት ከገንዘብና ጉልብትም ባለፈ መስዋእትነት ጭምር የተከፈለበት የኢትዮጵያዊያን የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ እና የስኬት ማሳያ መሆኑም ይታወቃል።
በዚህ የረጅም አመታት ጉዞ የባንዳ እና የባዳዎች የማሰናከል አጀንዳ ፈተና ቢሆንም በመንግስት በሳል የዲፕሎማሲ ጥረትና ጠንካራ የአመራር ጥበብ የሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ ተችሏል።
በግድቡ የግንባታ ሂደት የህዝቡ የላቀ ተሳትፎና የመንግስት ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሌት ከቀን የሀገሩ ዘብ ሆኖ በመቆም የላቀ ሚናውን መወጣቱን የሰራዊቱ አባላት ተናግረዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው የሰራዊት አባላት መካከል ምክትል መቶ አለቃ አብርሃም በሬ፤ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ሰራዊቱ ከገንዘቡና ጉልበቱም ባለፈ የሀገሩ ዘብ በመሆን የህይወት መስዋእትነት ጭምር የከፈለበት መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ሰራዊት በጀግንነቱና በሀገር መከታነቱ የሚታወቅ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ለሀገሩ ብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም ለህዝብ ደህንነት በአስተማማኝ መከታነቱ ይቀጥላል ብለዋል።
መሰረታዊ ወታደር ስመኝ ወርዶፋ፤ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ መከላከያ ሰራዊት ቦንድ በመግዛትና አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ጭምር የደም አሻራውን ማኖሩን አንስታ የሀገር አለኝታነታችን ይቀጥላል በማለት አረጋግጣለች።
ሌላው መሰረታዊ ወታደር ሄኖክ ወልዴ፤ የሕዳሴውን ግድብ ለማሳካት ኢትዮጵያዊያን በህብረ ብሄራዊ አንድነት የቆሙበትና ሰራዊቱን የላቀ ሚናውን የተወጣበት የጋራ ስኬት ውጤት መሆኑን አንስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)) በጉባ በነበራቸው ወግ የህዳሴ ግድብ ለረዥም ጊዜ የነበረን በደልና የድህነት ቀንበር የሚያስቆምና አዲስ ነገርን እንድናይ የሚያስችል ስለመሆኑ መግለፃቸው ይታወሳል።