በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል
አዳማ ፤ጳጉሜን 1 /2017 (ኢዜአ)፡-.በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የህብረተሰብ ጤና የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ግምገማና የያዝነው በጀት ዓመት እቅድ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት እንደ ሀገር ወባን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ሂደት የተሳካ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በተለይም ለወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቶ አስፈላጊውን የመከላከል ስራ መስራት መቻሉ ውጤት ስለማምጣቱ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና አጋር አካላት ተቀናጅተን ተላለፊ በሽታዎች የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ጥረት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የወባ ስርጭትንና ሌሎችም ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ የተሳካ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቅድመ መከላከልና የተሟላ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጭምር ብዙ መሰራቱን አንስተው በቀጣይም የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በክልሉ ተላለፊ በሽታዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም ሃላፊው አረጋግጠዋል።