በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርገዋል።
መቻል ሃዋሳ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።
ትዕግስት ወርቁ እና ቤተልሄም መንተሎ በጨዋታ ብርቄ አማረ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
ታሪኳ ጴጥሮስ ለሃዋሳ ከተማ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
በሌላኛው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዳግማዊት ሰለሞን እና ብርሃን ገብረስላሴ ግቦች ባህር ዳር ከነማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ትናንት 55ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጦ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ መርሃ ግብር ዛሬ ቀሪው የጨዋታ ጊዜ ተከናውኖ ትናንት በነበረበት የድሬዳዋ ከተማ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።
የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።