ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተባበረ ክንድና በጽናት የመፈፀም አቅማችን የታየበት ሁነኛ ማሳያ ነው- የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች

ጊምቢ፤ ጳጉሜን 1/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተባበረ ክንድና በጽናት የመፈፀም አቅማችን የታየበት ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው በህብረ ብሄራዊ አንድነት በጋራ ቆመው የገነቡት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

የግድቡ ግንባታ እውን መሆን የኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት የሚነግርና ሀገራዊ የእድገትና የብልፅግና ጉዞ ስኬት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢዜአ ሪፓርተር ያነጋገራቸው በምዕራብ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተባበረ ክንድና በጽናት የመፈፀም አቅማችን የታየበት ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉ አንስተዋል።

በዞኑ የጊንቢ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደረጄ ተመስገን፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዘመናት ቁጭት አብቅቶ በስኬት የተጠናቀቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለግድብ ግንባታ ከጅምሩ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደረጉ እንደነበሩ አስታውሰው፤ ግንባታው ተጠናቅቆ ለምርቃት ዝግጁ በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።

በዞኑ የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ምትኩ ሹማ፣ አቶ ሞኮንን አንገሬ እና  አለማዮ አዱኛ፤ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት በፅናትና በትብብር የተገነባ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል። 

የግድቡ ግንባታ መሳካት የኢትዮጵያን የመቻል አቅም ያሳየና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን ያረጋገጠ ፕሮጀክት ስለመሆኑም አንስተዋል። 

ሌላኛው የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ መለሰ ፎሎ፤ በህዳሴ ግድብ ስኬት ሁላችንም ተደስትናል፤ ለሌሎች የልማት ስራዎችም ድጋፍና ተሳትፏችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም