ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ኢትዮጵያዊያን ይቻላልን በተግባር ያሳዩበት የሚያኮራ ውጤት ነው- አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ኢትዮጵያዊያን ይቻላልን በተግባር ያሳዩበት የሚያኮራ ውጤት ነው- አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)
አርባ ምንጭ፤ ጳጉሜን 1/2017(ኢዜአ)፡ -ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ኢትዮጵያዊያን ይቻላልን በተግባር ያሳዩበት የሚያኮራ ውጤት መሆኑን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ከስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር በሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ የ"ሕዳሴ ሳምንት" መረሐ ግብር በአርባምንጭ ከተማ እያከናወነ ይገኛል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ ባደረጉት ንግግር፤ የግድቡ ግንባታ ከአድዋ ቀጥሎ የሕዝብና የመንግስት ቅንጅት ጎልቶ የታየበት የሀገር ሀብት መሆኑን አንስተዋል።
የውጭ ብድር መከልከሉ ኢትዮጵያውያን አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግድቡ ግንባታ ስኬት ኢትዮጵያዊያን ይቻላልን በተግባር ያሳዩበት የሚያኮራ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ይበልጥ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የታደለቻቸው የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ያስከተለብንን ቁጭት በሕዳሴ ግድብ ዕውን ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ግድቡ በኢትዮጵያዊን የእንችላለን መንፈስ ያሰረፀ ነው ብለዋል።
ከግድቡ ፕሮጀከት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የሄደችበት ቀጣናዊ እና አለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች የሀገሪቱ በሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ውጤት እንደሆነም ተናግረዋል።
የአርባምንጭ መረሃ ግብርም የሕዳሴን ጉዞ ለመዘከር እና ስለ ነገ ተወያይቶ የጋራ ጉዳይ ላይ ለመተባበር መሆኑን አንሰተዋል።
የሕዳሴ ግድብ ስኬት የሕዝቡ ጥረትና የፅናት ምልክት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብደላ ከማል (ዶ/ር) ናቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑ ታምኖበት በተፈጠረው ጽናት ለፍፃሜ መድረሱ ተጨማሪ ሞራል ፈጥሯል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ መሳካት በቀጣናው የኢትዮጵያን ተሰሚነት የሚያጎላ በመሆኑ ዩኒቨርሲስቲው ከዚሕ ቀደም ሲያደርግ የቆየውን ሙያዊ እና የሀብት ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።