ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ስኬት ትልቅ ብስራት ነው - አቶ ጥራቱ በየነ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ስኬት ትልቅ ብስራት መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ ገለፁ።

አቶ ጥራቱ በየነ ለኢዜአ እንዳሉት÷ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀም ሲደረግ የነበረውን ከፍተኛ ጫና በመቋቋም ግድቡን በራስ አቅም እውን ማድረግ መቻሉ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጥረትና ህብረት የህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ መቻላቸው ተጨማሪ የልማት ስራዎችን ለማሳካት መነሳሳትን የሚፈጥርላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የብልጽግና ጉዞዋን እንዳታሳልጥ እንቅፋት ለሚሆኑ አካላት ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጸጋ የተቸራት መሆኗን በመጥቀስ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵዊያንን ጽናት ያሳያ ትልቅ የኩራት ምንጭ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግድቡ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሰጡት ቆራጥ አመራርና ክትትል በትውልድ ሲታወስ የሚኖር ታሪካዊ አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማሳለጥ ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ መልካም አጋጣሚ ይዞ መምጣቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፤ የህዳሴ ግድቡ በሁሉም ትብብር የተሠራ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል፡፡ 

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳታፊ የሆኑ ሰራተኞች ያለእረፍት 24 ሰዓት በመስራት አሻራቸውን በማሳረፍ ጽናታቸውን ያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም